Abstract:
አረሞች ከሰብሎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ለሰብሎች ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን ውሃ ቦታና የፀሃይ ብርሃን በመሻማት ምርትንና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀነስ ያደርጋሉ፡፡ በጅማ ምርምር ማዕከል በተደረገ ጥናት በአረም ምክንያት የቡና ምርት ከ6ዐ እስከ 9ዐ በመቶ ሲቀንስ እንደሚችል ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪ በጌራ መለስተኛ ምርምር ማዕከል በተደረገ ጥናት በአረም ምክንያት የቡና ፍሬ ፈርጣማነት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀነስ እንደሚችል ተረጋግጧል፡፡ የሃገራችን ዋና ዋና ቡና አብቃይ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ በተራዘመ ጊዜ የሚያገኙ ስለሆነ ለቡናውም ዕድገት ሆነ ለአረሞች ዕድገት ተስማሚ ስለሆነ የቡና ሥራ ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ የሆነ የአረም ቁጥጥር የሚፈልግ በመሆኑ ለአረም ቁጥጥር የሚውለው በጀት ከፍተኛ ነው፡፡ በሰፋፊ የባለሃብቶች የቡና ማሳዎችም ሆነ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተደጋጋሚ የአረም ምንጣሮና የመድኃኒት ርጭትት ይከናወናል፡፡ እነዚህን አረሞች ለመከላከል የተለያዩ የአረም መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ዘዴዎች አንዱ ፀረ-አረም መድሃኒቶችን መጠቀም ነው፡፡ በጅማ ምርምር ማዕከል በተሰራ ጥናት በመሬት ውስጥ መራቢያና ምግብ ማከማቻ ሥራሥር ያላቸውን አረሞች በገጀራና በቁፋሮ ለመከላከል መሞከር አረሞቹን ከማራባት የዘለለ ጥቅም እንደሌለው ታውቋል፡፡ ፀረ-አረም መድሃኒቶችን ለመጠቀም መታወቅ ያለበት ጉዳይ ፀረ-አረሞች መርዛማ መሆናቸውንና በጥንቃቄ ካልተጠቀምንባቸው በሰው በእንስሳት በአጠቃላይ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትሉ የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡