Abstract:
በትሮፒክስ ውስጥ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ ታዳጊ ሀገሮች የሚካሄድ የእንስሳት እርባታ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የመኖ እጥረት እንደሚገጥመው የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንንም ችግር ለማቃለል የጥምር ግብርና በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሰብል ተረፈ-ምርትን ለመኖነት ማዋል የተለመደ አሰራር ነው፡፡ የሀገራችን የሰብል ተረፈ-ምርት መኖዎች አጠቃቀም ብንመለከት እስከ 5ዐ% የሚሆነውን ዓመታዊ የእንስሳት መኖ ፍጀታ የሚሸፍነው ከሰብል የሚገኘው ተረፈ-ምርት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሀገራተን በስፋት ከሚመረቱት የሰብል ዓይነቶች መካከል ተረፈ-ምርታቸው ለመኖነት በቀዳሚነት የሚውለው የጤፍ ጭድ፣ የገብስ እና የስንዴ ገለባ፣ እንዲሁም የበቆሎና የማሽላ አገዳ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ዓይነት የመኖ ምንጮች በተፈጥሯቸው ዝቅተኛ የሆነ የአልሚ ምግብና ከፍተኛ የጭረት ይዘት ያላቸው በመሆኑ በእንስሳት የተበይነትና በሆድዕቃ የተፈጭነት ደረጃቸው አነስተኛ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ የተረፈ-ምርት መኖዎችን አጠቃቀም ብክነት ከማስከተሉም በላይ የእንስሳቱን ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አስጠብቆ ለማስቀጠል ያዳግታል ስለሆነም የእንስሳት ምርታማነት ለመጨመር የሰብል ተረፈ-ምርት መኖዎችን ተበይነትና ተፈጭነት በኬሚካላዊ ዘዴ ማሻሻል አንደኛው የተረጋገጠ አማራጭ መንገድ ነው፡፡