Abstract:
አገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ስላላትና ቁጥሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የምግብ ዋስትናን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ደግሞ ከሰብል ምርት ባልተናነሰ መልኩ በአነስተኛ መሬትና በመካከለኛ ወጭ ሊረቡ የሚችሉ እንስሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ የስጋ ዶሮ ዕርባታ ለመጀመር ከፍተኛ ወጭን ከሚጠይቁና ምርታቸውም በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚዎች መድረስ የሚችሉ የእንስሳት እርድታ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ዘመናዊ የሥጋ ዶሮ ዕርባታ በተገቢው ሁኔታ የተከናወነ እንደሆነ ዶሮዎች ከ45 ቀን ባልበለጠ ጊዜ አስከ 2 ኪሎ ግራም የሚደርስ ዕድገት ያላቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዕርድ የሚደርሱ በአሆኑ በአመት አስከ 6 ዙር በማርባት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የሥጋ ዝርያዎች ተገቢ የሆነ አንክብካቤ ከመፈለጋቸው በተጨማሪ ዕድገታቸውን ሊያፋጥን የሚችል በሃይልና በፕሮቲን የንጥረ-ምግብ ይዘት የበለጸገ መኖ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንደ እንቁላል ዶሮ ዕርባታ ሁሉ በሥጋ ዶሮ ዕርባታ ውስጥ የመኖ ወጭ ድርሻ እስከ 7ዐ ከመቶ ይደርሳል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ዶሮዎች በተገቢው ሁኔታ የተዘጋጀ የተመጣጠነ መኖ መመገብ ያለባቸውና መኖውን ለማዘጋጀት የሚውሉት ጥሬ ዕቃዎችን ዋጋ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የመኖ ግብዓቶች ለሰው ምግብነት የሚውሉ አንዳንዶቹ ደግሞ በፋብሪካ የሚዘጋጁ በመሆናቸው ዋጋቸው ውድ ነው፡፡ የሥጋ ዶሮ ዕርባታን በማከናወን ጠቀም ያለ ትርፍ ለማግኘት የሚቻለው በጥራት የተሻሻለና በዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ የሥጋ ዶሮ መኖ ቀመሮ በማዘጋጀት ነው፡፡