Abstract:
አገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ስላላትና ቁጥሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የመግብ ዋስትናን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ደግሞ ከሰብል ምርት ባልተናነሰ መልኩ በአነስተኛ መሬት በመካከለኛ ወጭ ሊረቡ የሚችሉ አንስሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ፡፡ የዕንቁላል ዶሮ ዕርባታ ለመጀመር ከፍተኛ ወጭን ከማይጠይቁና ምርታቸውም በአነስተኛ ለተጠቃሚዎች መድረስ የሚችሉ የእንስሳት ዕርባታ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ዘመናዊ የእንቁላል ዕርባታ በተገቢው ሁኔታ የተከናወነ እንደሆነ ከፍተኛ የእንቁላል ምርት ከማስገኘቱም ባሻገር ምርት በሚያቆምበት ወቅትም የአገራችን ተጠቃሚዎች የሚፈለጉት ዓይነት የዶሮ ሥጋ ይሰጣሉ፡፡
በአለማችን ላይ የተለያዩ ምርታማ የሆኑ የእንቁላል ዝርያ ዶሮዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ዶሮዎች ለበርካታ አመታት የዝርያ ማሻሻያ ሥራዎች የተካሄደባቸው በመሆናቸው በአንድ አመት ውስጥ ከ3ዐዐ እንቁላል በላይ ለማምረት ይታወቃሉ፡፡ የምርት ጊዜያቸውን በሚያጠናቅቁበት ወቅት ለዕርድ አገልግሎትም ይውላሉ፡፡ ይህንን ከፍተኛ ምርት ለማግኘት እነዚሁ ዘመናዊ የእንቁላል ዶሮ ዝርያዎች የተሻሻለ አመጋገብ መጠለያና የጤና ዕንክብካቤ ያስፈልጋል፡፡ ዕርባታውን በተገቢ ሁኔታ ለማስኬድም መሰረታዊ የዕንቁላል ዶሮ ዕርባታ ዕውቀትና ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡