Abstract:
የቅንጬ አረም የመጀመሪያ መገኛ ቦታ ናቸው ተብለው ከሚታወቁ የሰሜንና የደቡብ አሜሪካ አካባቢዎች ውስጥ ሜክሲኮ ትሮፒካል አሜሪካ እና ዌስት ኢንዲስ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ አረሙ ከእነዚህ አካባቢዎች በመነሳት ባለፉት 1ዐዐ አመታት ውስጥ ወደ አውስትራሊያ እስያና አፍሪካ እንደ ሰደድ እሳት በመዛመት በርካታ አካባቢዎችን ሸፍኖ ይገኛል፡፡የአረሙ ወረራና መስፋፋት መጀመሪያ በቅሎ ከነበረበት አካባቢ በይበልጥ በአዳዲስ ቦታዎች ላይ ተባብሶ ይታያል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት አረሙ ወደ ሌላ አካባቢዎች ሲዛመት አረሙን አስተዳደግ በመሻማትና ብቅለቱን በመግታት የሚታወቁ ነፍሳትና በሽታ አምጪ ተሀዋስያን ባለመኖራቸው ወይም በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ በተወረሩ ቦታዎች ላይ ሊከሰቱ ባለመቻላቸው ነው፡፡ በስፋት በመከሰት መጀመሪያ በታወቀባቸው አህጉራት ውስጥ አረሙ በሁለት ዋና ዋና ዝርያዎች እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ዝርያዎች የሰሜን አሜሪካ የቅንጩ አረም ዝርያ አና የደቡብ አሜሪካ የቅንጬ አረም ዝርያ በመባል ይታወቃሉ፡፡የደቡብ አሜሪካ የቅንጬ አረም ዝርያ ትላልቅ ቢጫ አበባዎችና የዘር መራቢያ ክፍሎች ሲኖሩት የሰሜን አሜሪካ ዝርያ ደግሞ በአነስተኛ ነጫጭ አበቦቹ ይታወቃል፡፡ በአረሙ ግንድ ላይ በተቀፅላ የሚያድጉት ቅርንጫፎቹም ከሰሜን አሜሪካ ዝርያ ጋር ሲነፃፀሩ አነስተኛ የዕድገት መጠን ያላቸው ናቸው፡፡ በደቡብ አሜሪካ ዝርያ ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር ሰስኩዊተርፔን ላክቶን (Sesquiterpene lactone) በመባል የሚታወቀው ሂሜኒን (bymenin) ሲሆን በሰሜን አሜሪካው ዝርያ ውስጥ የሚገኘው ደግሞ ፓርቴኒን (partheniu) ነው፡፡ ዛሬ በሀገራችን አና በብዙ የዓለም አካባቢዎች ተሰራጭቶ የሚገኘው ቅንጬ አረም አስራ አምስት ዝርያዎች እንዳሉት ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ የእነዚህም ዝርያዎች የመጀመሪያ መገኛ ቦታዎች አዚያው ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ነው፡፡