Abstract:
ቡና ቋሚ ተክል እንደመሆኑ መጠን ዘላቂና አስተማማኝ ምርት ለማግኘት ጠንካራ ዛፍ ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ ጠንካራና ከፍተኛ ምርት ሊሰጥ የሚችል የቡና ተክል ለማልማት አስቀድሞ ከጥሩ ዘር ተመርጦ የፈላና ጤናማ የሆነ ችግኝ መትከል ወሳኝነት አለው፡፡
ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ ብቸኛው መንገድ ባህላዊውን የአሰራር ዘዴ በዘመናዊ መልክ መቀየር እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም ይህ ጽሑፍ በአገራችን በቡና ችግኝ ጣቢያ የተገኙ የምርምር ውጤቶችን የተሻሻሉና ዘመናዊ የአሰራር ዘዴዎችንና ከልምድ የተገኙት ጠቃሚ እውቀቶችን በማካተት ቡና አብቃዩ ህብረተሰብ ጥሩ አቋም ያለው ችግኝ ማፍላትና የቡናውም ምርታማነት ማሳደግ እንዲችል ታስቦ በቀላልና በሚገባ መንገድ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በአገራችን ወደፊት የሚለሙም ሆኑ በመልማት ላይ ያሉ ሰፋፊ አርሻዎችና አነስተኛ የገበሬ ይዞታዎች ዘመናዊ መልክ እንዲኖራቸው ይህ የቡና ችግኝ አመራረት መመሪያ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡