Abstract:
በሀገራችን በስፋት የሚመረቱት የአገዳ ሰብሎች ውስጥ ማሽላ አንዲ ሲሆን ተረፈ ምርቱን ጨምሮ ለተለየዩ ጥቅሞች ይውላል፡፡ በማሽላ ላይ ጥቃት በማድረስ የሚታወቁ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ነፍሳት ተባዮች የተመዘገቡ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፉ የመጣው የማሽላ ጥንዚዛ Sorghum chafer Pachnoda interrupta (Olivier) በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ ጥንዚዛው ከብዙ አመታት (4ዐ-50 አመት) በፊት ይታይ እንደነበር ቢታወቅም ከ1986 ዓ.ም. ወዲህ ግን በየአመቱ በተከታታይ በመከሰት በተለያዩ ሰብሎች ላይ /ማሽላ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ አደንጓሬ፣ ሱፍ ወዘተ/ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡ ስርጭቱም በ4 ክልሎች /አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እና ድሬደዋ/ በ11 ዞኖች በ39 ወረዳዎች እና በ387 ቀበሌዎች እንደተስፋፋ የ1992/93 ምርት ዘመን መረጃ ያመለክታል፡፡ ተባዩ በሰብል ላይ ጉዳት በማድረስ በተከሰተበት በ1986 ዓ.ም. በአንድ ወረዳ እና በአንድ ቀበሌ ብቻ እንደታየ የሚታወስ ነው /ሠንጠረዥ ቁ. 1 እና ስዕል 1/፡፡ ይህ ተባይ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ገበሬው በዘልማድ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች /ጭስ ማጨስ፣ ማሽላውን ከስር በመስበር ማጋደም በእጅ መልቀም/ በተጨማሪ የተለያዩ ፀረ-ተባዮችን በመርጨት እና በመለወስ ለመከላከል ቢመከርም የተባዩን ቁጥር ለመቀነስ እና ስርጭቱን ለመግታት አልተቻለም፡፡ ተባዩ ከሌሎች ነፍሳት ተባዮች ለየት ባለ ሁኔታ ለረጅም ቀናት /እስከ 2 ወር/ በተከታታይ የሚከሰት ሲሆን ከሰብል ማሳ ውጭ በአብዛኛው ከሰው ንክኪ አካባቢዎች በስፋት መሰራጨቱ የመከላከሉን ተግባር አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ተባዩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የሚደረግ መከላከል ስለሌለ ለተባዩ በፍጥነት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይገመታል፡፡